ሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር ያገኛቸውን የሰብል ዝርያዎች እያባዛ ነው
ጎባ ታህሳስ 5 /2013 (ኢዜአ) ሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር ያገኛቸውን የሰብል ዝሪያዎችን አርሶ አደሩ ጋር እንዲደርሱ በማባዛት ላይ እንደሚገኘ ገለጸ፡፡
ማዕከሉ በምርምር ጣቢያና አርሶ አደሩ ማሳ ላይ እያባዛቸው የሚገኙ  የሰብል ዝሪያዎች  ባለድርሻ አካላት ትናንት በመስክ  ተመልክተዋል፡፡
በማዕከሉ የቅባትና ጥራጥሬ ሰብሎች ቡድን መሪና ተመራማሪ አቶ ጌታቸው አሰፋ  በወቅቱ እንደገለጹት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትናና ምርታማነትን የሚያሳድጉ
 ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረጉ ነው።
በተለይ የአርሶ አደሩ የዘመናት ጥያቄ የነበረውን የጥራጥሬ ዝሪያዎች አቅርቦት ለማዳረስ  ደርቤራ፣ ሶሬሳና  ኬና የሚባሉ አምስት የጥቁር አዝሙድና ሁንዳ ኦል፣ ኤቢሳና ቡርቃ
የሚባሉ የአብሽ ዝሪያዎችን በኩታ ገጠም  በማልማት በማባዛት ላይ እንደሚገኘ ገልጸዋል።
ዝርያዎቹ በሽታንና ድርቅን በመቋቋም የተሻለ ምርት እንደሚሰጡ በብሔራዊ የዝሪያ አጽዳቂ ኮሚቴ ተገምግመው የተለቀቁ መሆናቸውንም ተመራማሪው አስታውቀዋል፡፡ 
የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ በሪሶ በበኩላቸው ማዕከሉ በሰብል፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህልና የእንስሳት መኖ  ጨምሮ  ከ80 የሚበልጡ
ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚው  ማድረሱን ገልጸዋል፡፡
በመስክ ምልከታው የተሳተፉት የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ቦጋለ   ማዕከሉ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በመጨመር ተጠቃሚ እንዲሆኑ
እያደረገ ያለውን  ጥረት ለመደገፍ እያገዙ መሆናቸውን ተናገረዋል፡፡
ቴክኖሎጂን ማፍለቅ ብቻውን ግብ አለመሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በምርምር የሚወጡ ዝርያዎችን አባዝቶ ለአርሶ አደሮችና በግብርና ኢንቨስትመንት ለተሰማሩ ባለሀብቶች
ተደራሽ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር  በቅንጅት በመስራት ላይ እንደሚገኙ  አስረድተዋል፡፡
መንግስት ከውጭ  የሚገቡ የሰብል ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ለማሳካትም የምርምር ማዕከላት  ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን  ተናግረዋል ።
የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል የተሻሻሉ ዝርያዎችን በቅርበት እንድናገኝ ከማድረግ ባሻገር ምርታማነትን ከሚጨምሩ የግብርና አሰራሮች ጋርም እንድንተዋወቅ ረድቶኛል ያሉት ደግሞ
የጎሮ ወረዳ አርሶ አደር መሐመድ ሁሴን ናቸው ።
የሲናና ወረዳ አርሶ አደር ከድር መሐመድም በበኩላቸው  ቀደም ሲል ከአንድ ሄክታር የአካባቢ ዝርያ የሚያገኙት ምርት አነስተኛ እንደነበር ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከማዕከሉ ያገኙትን ምርጥ ዘር  ከተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች ጋር  በመተግበር ስንዴ በአማካይ በሄክታር እስከ 50 ኩንታል በማምረት ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ የሚገኙ የሲናናን ጨምሮ 17  የግብርና ምርምር ማዕከላት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣ በማላማድና በማሰራጨት አርሶ አደሩን እየደገፉ መሆናቸው ተመለክቷል፡፡